SUNDAY, 26 AUGUST 2012
BY ZEKARIAS SINTAYEHU
ባለፈው ማክሰኞ ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ ስልክ የተደወለው በጣም በጠዋት ነበር፡፡ የስልክ መልዕክቱም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት ሕይወት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይፋ ሊደረግ እንደሆነ የሚገልጽ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ1፡00 ሰዓት የዜና እወጃው ላይ የዕለቱ ተረኛ ዜና አንባቢ በረጅሙ ከተነፈሰ በኋላ በርካቶችን ያስደነገጠውን፣ ያሳዘነውንና ታሪካዊ የሆነው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዜና ዕረፍት እንባ እየተናነቀው አነበበ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕልፈተ ሕይወት አስመልክቶ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ተነበበ፡፡ በመግለጫው ኢትዮጵያን ላለፉት 21 ዓመታት ሲመሯት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ሰኞ ከምሽቱ 5፡40 ሰዓት ላይ በድንገት ማረፋቸው ተገለጸ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ ቴሌቪዥኑ የእሳቸውን የተለያዩ ፎቶግራፎች እያሳየ በዋሽንት የተቀነባበረ የሐዘን እንጉርጉሮ ሙዚቃን ማሰማቱን ቀጠለ፡፡ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም የሬዲዮ ጣቢያዎች ፍጹም ሐዘን ውስጥ የሚከቱ የሐዘን እንጉርጉሮ ሙዚቃዎችን ማሰማታቸውን ቀጠሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ማክሰኞ ጠዋት የደረሳት መርዶ ከክረምቱ ዝናብና ብርድ ጋር ተጨምሮ ዜጐቿን ሐዘንና ትካዜ ውስጥ ጨመራቸው፡፡ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ በጠዋቱ በርካታ ዜጎች ፊታቸው ላይ በግልጽ የሚነበብ ሐዘን ይታይ ነበር፡፡ በማለዳ ወደሥራቸው የሚያመሩ ዜጎች ጆሯቸውን በጥቋቁር የጆሮ ማዳመጫዎች ደፍነው የመሪያቸውን የሞት ዜና በስልካቸው ሬዲዮ ሲከታተሉ ተስተውለዋል፡፡ አንዳንዶችም ሁለትና ከዚያ በላይ እየሆኑ ተሰብስበው አስደንጋጭና ድንገተኛ የሆነውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕልፈት ያዳምጡ ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ የሰሙትን ዜና ለወዳጆቻቸውና ለቤተሰቦቻቸው እየደወሉ ሲናገሩ ነበር፡፡ ብቻ ማክሰኞ ጠዋት በአዲስ አበባ መንገድ ላይ ይታዩ የነበሩ ዜጎች ከስልካቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት በጣም ቅርብ ነበር፡፡ ታክሲ ላይ የነበረውም ድባብ የሐዘንና የድንጋጤ ነበር፡፡ የታክሲው ሬዲዮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜና ዕረፍት ከተሰማ ጀምሮ በዋሽንት የተቀናበረውን የሐዘን እንጉርጉሮ ሙዚቃ ያሰማል፡፡ ተሳፋሪዎቹም በፀጥታ ሙዚቃውን ያዳምጣሉ፡፡ የታክሲው የመጨረሻ ወንበር ላይ ያሉት ወጣቶች ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማውራት ጀመሩ፡፡ ወጣቶቹ ያልጠበቁት ዜና መሆኑን እየተወያዩ የሕልፈቱ ዜና እንዳሳዘናቸው ይነጋገራሉ፡፡ ከአጠገቤ የተቀመጠው ግለሰብ ወጣቶቹ የሚያወሩት ዜና እውነትን ጠይቆኝ ሳረጋግጥለት፣ አማትቦ ወዲያው ስልኩን አወጣ፡፡ ያው እሱም ከስልኩ ጋር ያለውን ቁርኝት ቀጠለበት፡፡ በአዕምሮው ለመጡለት ወዳጆቹ እየደወለ ዜናውን ማሰማቱን ተያያዘው፡፡ የአዲስ አበባ ዜጐች ማክሰኞ ረፋድ ላይ በአንድነት ሲያደርጉት ከተስተዋሉት ጉዳዮች መካከል ከስልካቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ቀዳሚነቱን ይወስዳል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜና ዕረፍት ወዲያው ፌስቡክንና ትዊተርን በመሳሰሉ ሶሻል ሚዲያዎች እንደ ሰደድ እሳት መሰራጨት ጀመረ፡፡ በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የፕሮፋይል ፎቶግራፎቻቸውን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶግራፎች ወዲያው ቀየሩ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት የተሰማቸውን ከፍተኛ ሐዘን እየገለጹ፣ በርካቶች ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን የሚመኙ ጽሑፎችን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አሰፈሩ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት በአገር ውስጥ ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫ ተቋማትም ጭምር ዋነኛ ዜና ሆኖ ተላልፏል፡፡ እንደ ቢቢሲና አልጄዚራ ያሉ ዓለም አቀፍ የዜና ጣቢያዎች የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሞት ከፍተኛ የአየር ጊዜ በመስጠት ቀኑን ሙሉ ሲያስተላልፉ ነበር፡፡ ዓለም አቀፎቹ የሚዲያ ተቋማት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከዚህ በፊት የሠሩትን ታሪክ እያወደሱ ከፍተኛ ሽፋን ሰጥተዋቸዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሕልፈትን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያረፉት ባጋጠማቸው የኢንፌክሽን ሕመም መሆኑን አስታወቀ፡፡ በሚኒስትር ማዕረግ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን በሰጡት መግለጫ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜና ዕረፍትን፣ ‹‹ከባድና እጅግ ዘግናኝ ዜና›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠበት የሒልተን ሆቴልም በመዲናይቱ ሲታይ የነበረው የሐዘን ድባብ ይታይበት ነበር፡፡ በሆቴሉም የተሰቀሉ ባንዲራዎች ዝቅ ተደርገው ሲውለበለቡ ታይተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ይገባል ተብሎ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተነገረ ሲሆን፣ በርካታ ዜጎች አስከሬኑን ለመቀበል ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጐርፉ ነበር፡፡ ሆኖም የአስከሬኑ መግቢያ ሰዓት ወደ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ተቀይሮ፣ በዚሁ ጊዜ የመለስን ፎቶ ያነገቡና የበሩ ጧፎችን የያዙ የመለስ ወዳጆች በቦሌ አካባቢ በእንባ ሲራጩ ታይተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫ ተቋማት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስከሬን ከብራሰልሱ ሴንት ሉክ ሆስፒታል ወደ አገራቸው ሲጫን ታይቷል፡፡ በመጨረሻም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ከምሽቱ 4፡20 ላይ ከአውሮፕላን ሲወርድ በርካታ ባለሥልጣናት በእንባ ተራጭተዋል፡፡ የአምስት ደቂቃው መንገድ ሦስት ሰዓት ፈጀባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለተለያዩ ስብሰባዎች ከአገር ሲወጡ እንዲሁም የሄዱበትን ስብሰባ አጠናቅቀው ወደ አገር ቤት ሲመለሱ አንድ ክስተት ሁሌ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቤተ መንግሥታቸው ወደ ቦሌ አሊያም ከቦሌ ወደ ቤተ መንግሥታቸው ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት የሚሄዱበት ጐዳና ሙሉ ለሙሉ ለእሳቸው ነፃ ይደረጋል፡፡ በዚህ መንገድ ዳርና ዳር የሚቆሙ መኪናዎች የሚነሱ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜም ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ ይደረጋሉ፡፡ በግምት በየአሥር ሜትሩ መሣሪያ ታጥቀውና ጀርባቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡ የፌዴራል ፖሊሶች በፍጹም ንቃት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በዓይናቸው ይቆጣጠራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር መንገዱ ዳር ባሉ ረዣዥም ሕንፃዎች ላይ አልሞ ተኳሾች በንቃት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በአየርና በምድር ጠባቂዎቹ ቁጥጥር ሥር መሆኑ እንደተረጋገጠ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጫነው መኪና እንደሮኬት እየተምዘገመዘገ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ጉዞውን ይጨርሳል፡፡ ይህ ክስተት በበርካቶች ዘንድ የሚታወቅና የሚታወስ ነበር፡፡ ሆኖም ባለፈው ማክሰኞ ምሽት አስከሬናቸው ከአውሮፕላን ከወረደ በኋላ በአውሮፕላን ማረፊያው ሠራተኞች በሕይወት እያሉ ሲመላለሱበት በነበረው መኪና ላይ ተጭኗል፡፡ በአውሮፕላን ማረፊያው አስከሬኑን ሊቀበሉ የሄዱት የከተማ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሐዘናቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከሁለት ሴት ልጆቻቸው ጋር ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ፣ መሬት ላይ ሲጠብቋቸው የነበሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት በእንባ ተራጭተዋል፡፡ ከዚያም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን በየመንገዱ ጧፍ ለኩሶና ፎቶግራፋቸውን ይዞ በሚጠብቃቸው ሕዝብ እየታጀበ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ቤተ መንግሥት አቅንቷል፡፡ በየመንገዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስከሬን ይጠብቅ የነበረው ሕዝብ በከፍተኛ ሐዘን ተቀብሏቸዋል፡፡ በርካቶችም ሐዘናቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ከሁለቱ የዓይን ጉድጓዶቻቸው ውስጥ የእንባ ዘለላዎች በጉንጮቻቸው ሲፈሱ ታይተዋል፡፡ አንዳንዶችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ጊዜ ብቻ በሕይወት ኖረው ሕዝቡ ለእሳቸው የነበረውን አክብሮት እንዲያዩት ተመኝተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕይወት ዘመናቸው አምስት ደቂቃ ይፈጅባቸው የነበረው መንገድ ግን ለአስከሬናቸው ሦስት ሰዓት ያህል ፈጅቶበታል፡፡ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለ21 ዓመታት የኖሩበት ቤት አስከሬናቸው እንደደረሰ ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ ክፉኛ አምርረው ሲያለቅሱ ነበር፡፡ ደረታቸውን እየደቁ መሪር ሐዘናቸውን ሲገልጹ የነበሩት ወይዘሮ አዜብ፣ መኖርያ ቤታቸው እንደደረሱ፣ ‹‹ቀጣሃኝ፣ ቀጣሃኝ፤ ቤታችን ደረስን አንተ ግን የለህም፤ ጌታዬ ጌታዬ፤›› እያሉ በባለቤታቸው ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡ ለወትሮ በአራት ኪሎ ቤት መንግሥት አካባቢ ወፍ ዝር የማይል ቢሆንም፣ ረዕቡ ላይ ግን የጥምቀተ ባህር ሜዳ ይመስል ነበር፡፡ ወደ ግቢውም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየገቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ሲገልጹ ነበር፡፡ የቤተ መንግሥቱ በር ክፍት መሆኑን የሰሙ ሰዎች፣ ከሐዘኑ ባሻገርም መሪያቸው የሚኖርበት ቤት ምን ይመስል? እንደሆነ ለማወቅ እንደገቡ ያሳብቅባቸዋል፡፡ በግቢው ውስጥ ትልቅ ነጭ ድንኳን ተጥሏል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ከቤታቸው የተቀመጠ ቢሆንም፣ ከድንኳኑ ፊት ለፊት በተቀመጠው ስክሪን ይታይ ነበር፡፡ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖርያ ግቢ መግባት የሚችሉት የቅርብ ዘመዶችና ባለሥልጣናት ብቻ ሲሆኑ፣ የከተማው ነዋሪ ከግቢው ውጪ ባለው ድንኳን እርሙን አውጥቶ ይሄድ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት በደረስንበት ወቅት ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ ወጣ ብለው ነበር፡፡ በቤታቸው ዙሪያ ባለው በረንዳ በርካታ ዘመድ አዝማዶችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተቀምጠው ይታያሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬንም ፊት ለፊት ያለው ክፍል ውስጥ በአበባና በሻማ ተከቦ ተቀምጧል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዳጆችና ጓደኞች ሲገቡ ከሚያሰሙት ለቅሶ ውጪ ብዙም ለቅሶ በግቢው ውስጥ አይሰማም ነበር፡፡ ሆኖም ግን በግቢው ውስጥ ከፍተኛ የሐዘን ድባብ ነበር፡፡ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ግቢው የደረሱት ወይዘሮ አዜብ የጀመሩት ለቅሶ ግን በርካቶቹን ሲያንፈቀፍቅ ነበር፡፡ ወይዘሮ አዜብ የባለቤታቸውን ስም እየጠሩ ሲያለቅሱ የነበረ ሲሆን፣ ልጃቸው ሰመሃልና ማርዳ ሊያረጓጓቸው ሲሞክሩ አሻፈረኝ ይሉ ነበር፡፡ በቤቱ ፊት ለፊት የተሰቀለውን የመለስ ፎቶ እያመለከቱ የሚያለቅሱት ወይዘሮ አዜብ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እህት ታጅበው ነበር፡፡ ‹‹እነዚያ ቀያይ እጆች ናፈቁኝ፤ በቴሌቪዥንም ላይ አይንቀሳቀሱም፤›› እያሉ ያለቅሱ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ እህት ነበሩ፡፡ ባለቤታቸውም እግዚአብሔርን እየተጣሩ፣ ‹‹አንድ ጊዜ ብቻ አንቀሳቅሰው፤›› ሲሉ በግቢው ውስጥ የነበሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የመለስ የቀድሞ ጓደኞችና ዘመድ አዝማዶች ክፉኛ ተላቅሰዋል፡፡ መለስ ዜናዊ ማን ናቸው? ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሚያዝያ 30 ቀን 1947 ዓ.ም. በትግራይ ክልል አደዋ ከተማ ከአባታቸው ከአቶ ዜናዊ አስረስና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዓለማሽ ገብረ ልዑል ተወለዱ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለተኛ
ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በትምህርታቸው በጣም ጐበዝ የሚባሉ ተማሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚም ነበሩ፡፡ በመሆኑም በየወሩ ከዚህ ድርጅት የገንዘብ ሽልማት ያገኙ ነበር፡፡ ገንዘቡን በአብዛኛው መጽሐፍ በመግዛት ያጠፉት እንደነበር የቅርብ ጓደኞቻቸው ይናገራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትምህርት ቤቶች መካከል በሚደረጉ ውድድሮች በአብዛኛው ጊዜ አሸናፊ እንደነበሩ በቅርብ የሚያወቋቸው ሰዎች ይገልጻሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሕክምና ትምህርታቸውን ለሁለት ዓመታት በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡ ከዚያም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በማቋረጥ የደርግ ሥርዓትን በትጥቅ ለመፋለም በረሃ ገብተዋል፡፡ መለስ በበረሃ ሕይወታቸው የሕወሓትን የፖለቲካ ክንፍ የመሩ ሲሆን፣ በጣም ታታሪ፣ ለሚሠሩት ነገር ራሳቸውን የሰጡና ከማንበብ በተጨማሪ ራሳቸውን በሚገባ መግለጽ የሚችሉ መሪ መሆናቸውን የቅርብ ጓደኞቻቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ጊዜ የሚወስድ ሥራን በፍጥነት በመጨረስ፣ አዳዲስ ሐሳቦችን በማፍለቅና በአዳማጭነታቸው ይታወቃሉ፡፡ በበረሃ የነበረው የሕወሓት እስር ቤት ጥራቱን ያልጠበቀ መሆኑን የተናገሩ ታሳሪዎን ሐሳብ በመቀበል ከቀድሞ የሕወሓት የወታደራዊ ክንፍ መሪ ስዬ አብርሃ ጋር በመሆን መለስ እስር ቤቱ በሜጀር ጄኔራል ኅየሎም አርዓያ ብርጌድ ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ እንዲገነባ ወስነዋል፡፡ መለስ ውሳኔ የመስጠት አቅማቸው ከፍተኛ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ አኅጉር በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቀውን የደርግ መንግሥት የፈረጠመ ወታደራዊ ኃይል በማፍረክረክ አስገራሚ የሆነ ድል ለመቀዳጀት ከትግል ጓዶቻቸው ጋር የሰጡት አመራር ገዝፎ ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር ለ25 ዓመታት በትዳር ቆይተዋል፡፡ በዚሁ ቆይታቸውም ሰመሃል፣ ሰናይና ማርዳ የተባሉ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ መለስ በሕወሓት አመራር አባልነት የደርግን መንግሥት ለ17 ዓመታት ከታገሉ በኋላ በድል አድራጊነት አዲስ አበባ በመግባት በሽግግሩ መንግሥት አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ፣ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሥልጣን እንደያዙ ብዙ የፖለቲካ ዕውቀት እንጂ እምብዛም የኢኮኖሚ ዕውቀት አልነበራቸውም ነበር፡፡ በመሆኑም አንድ በበረሃ ያውቃቸው የነበረ ምዕራባዊ የደኅንነት ኃላፊ ከኢትዮጵያ ከመውጣቱ በፊት ሊሰናበታቸው ሄዶ፣ መሠረታዊ የኢኮኖሚክስ ዕውቀት የሚሰጡዋቸውን መጻሕፍት እንዲሰጣቸው ጠይቀውታል፡፡ የደኅንነት ኃላፊውም ከኤምባሲ ያገኛቸውን በርካታ የኢኮኖሚ መጻሕፍት እንደሰጣቸው ተናግሯል፡፡ እንግዲህ አሁን መለስ ያላቸው የኢኮኖሚ ዕውቀት የተጀመረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ መለስ ያላቸው ራዕይ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተብሎ በሁለት ጐራ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ የኢኮኖሚ ራዕያቸው በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው የአምስት ዓመቱን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ያካትታል፡፡ መለስ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ከአፍሪካ አልፎ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ በማድረግ ሲታወቁ፣ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ግሽበትም መስተዋሉ አይዘነጋም፡፡ በተፃራሪው የመለስ በአገር ውስጥ የሚያራምዱት የፖለቲካ ራዕይ ያልሰፋና ትግበራ ላይም ችግር ያለበት ነው እየተባለ ይተቻል፡፡ የመለስ መንግሥት በሰብዓዊ መብት አከባበር፣ በዲሞክራሲ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሙስናና በፍትሕ ሥርዓቱ ሁኔታ ይተቻል፡፡ በተለይም የመለስ መንግሥት የመናገር ነፃነትንና ሚዲያን ያፍናል በመባል በምዕራብያውያን ክፉኛ ይተቻል፡፡ ምንም እንኳን እሳቸውና መንግሥታቸው ባይቀበሉትም፡፡ በተቃራኒው የመለስ መንግሥት ከምዕራባውያን ከፍተኛ ዕርዳታ የሚያገኝ መንግሥት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አፍሪካን በመወከል በበርካታ ስብሰባዎች ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ በኔፓድና በአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን ወክለው በመደራደር የአፍሪካ ድምፅ እየተባሉ እስከመጠራት ደርሰዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ ሕዝቡ ከፍተኛ አክብሮት ለእሳቸው ያሳየ ሲሆን፣ አቶ በረከት ሕዝቡ ያስተላለፈውን መልዕክት በሚገባ አግኝተነዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በፓርቲው ውስጥ ክፍፍል የሚባለው ነገር የማይታሰብ መሆኑን የገለጹት አቶ በረከት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ ለማስፈጸም ኢሕአዴግ በእልህ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ አሁን የተጋረጠበትን ወሳኝ ችግር ማለፍ ከቻለ ወደፊት የሚገጥሙትን ፈተናዎች በቀላሉ ማለፍ ይችላል ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ያልተሰሙ የመለስ ታሪኮች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሽግግሩ ዘመን በሰጡት አንድ መግለጫ ላይ ባንዲራ ጨርቅ መሆኑን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ንግግራቸውም በርካቶች መለስ የአገር ፍቅር እንደሌላቸውና ባንዲራውን እንዳዋደቁት ቆጥረዋቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተጠይቀው፣ ይቀርፃቸው የነበረውን ካሜራ አስጠፍተው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ባንዲራ ጨርቅ ነው፤ ይህ በሁሉም ሰው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ባንዲራ ጨርቅ ሆኖ ሳለ መለስ ሲለው ጨርቅ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሕይወታቸው አሳዛኝ ስለሚሏቸው ገጠመኝ ተጠይቀው ሦስት ነገሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ “የመጀመሪያው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የቀረበለትን የሰላም ሐሳብ አልቀበልም፣ አሻፈረኝ በማለቱ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተሰው ዜጐች ሁሌም ያሳዝኑኛል፡፡ ሁለተኛው በምርጫ 97 ጊዜ በተፈጠረው ግርግር ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ናቸው፡፡ በወቅቱ እኔ እንደ ግለሰብ ብሞት እንኳን ምንም አይሰማኝም፡፡ ሆኖም እኔ የአገር መሪ እንደመሆኔ መጠን በሰላም ሳይሆን በእንደዚያ ዓይነት ግርግር ሥልጣን ብለቅ አገሪቱ
ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ልትገባ ትችል ነበር፡፡ በመሆኑም ያ ውሳኔ ቢያሳዝነኝም ማንም በእኔ ቦታ ቢሆን የሚያደርገው ነገር ነበር፡፡ ሦስተኛ የሚያሳዝነኝ ጉዳይ የሕክምና ትምህርቴን ስከታተል አውቀው የነበረው አንድ ሻይ ቤት ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተመልክቼው ምንም ዓይነት ለውጥ ባለማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡ አገሪቱን ለመለወጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተረድቼ የበለጠ ለመሥራት ወስኛለሁ፤” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብዙ ጊዜ ሲስቁ ስለማይታዩ፣ ለምን? እንደማይስቁ ተጠይቀው “ለምን እስቃለሁ” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡ “እኔ ቢሮ ውስጥ ሆኜ በየቀኑ የማነባቸው ደብዳቤዎች በሰቆቃ የተሞሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት በደል ደርሶብኛል፣ ፍትሕ አጣሁ፣ ያሰርካቸውን ሰዎች ፍታ፣ የሚሉ በርካታ ይህን መሰል ደብዳቤዎች ይደርሱኛል፡፡ አብዛኞቹም ሁሉን ነገር የማደርገው እኔ እንደሆንኩ የሚገልጹ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ በአገሪቷና በአካባቢው ያሉትን በርካታ ችግሮች ለመፍታት በየጊዜው እታገላለሁ፡፡ ታዲያ ምን የሚያስቅ ነገር ኖሮ ነው የምስቀው፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አብዛኛው የሕይወት ዘመናቸውን በሥራ ያሳለፉና ለሚሠሩት ሥራ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በቢሯቸው የሚያጠፉ ሲሆን፣ ማንበብና መጻፍ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው፡፡ መለስ በቤታቸው በሚገኘው ቢሯቸው በምሽት ጊዜ የሚሠሩ ሲሆን፣ እንቅልፋቸውንም የሚተኙት እዚያው የሚያነቡበት ጠረጴዛ ላይ ተደግፈው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ብዙ ጊዜም ጠባቂዎቻቸው ይህን ልምዳቸውን ስለሚያውቁ እንቅልፍ ሲያሸልባቸው ከጠረጴዛቸው ላይ አንስተው ወደ መኝታ ክፍላቸው ይወስዷቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብዙም የዕረፍት ጊዜ ባይኖራቸውም የሜዳ ቴኒስ መጫወት ያስደስታቸዋል፡፡ ቀጣዩ የኢትዮጵያ መሪ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ሕልፈተ ሕይወት ተከትሎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በሙሉ ሥልጣን አገሪቷን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በዕረፍት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን ለማፅደቅ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ስብሰባ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም፣ ስብሰባው ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፣ አስቸኳይ ስብሰባው ላልተወሰነ ጊዜ የተራዘመው የአቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር በዚያው ቀን ስለተፈጸመና ተደራራቢ ሥራዎች በማጋጠማቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ የፓርቲው ሊቀመንበርም በየጉባዔው ይመረጣል፡፡ ቀጣዩና ዘጠነኛው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ በቅርቡ የሚካሄድ ሲሆን፣ ፓርቲው በጉባዔው ሊቀመንበሩን እንደሚመርጥ ይጠበቃል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን አቶ ኃይለ ማርያም የድርጅቱንና የመንግሥትን ሥልጣን ይዘው ይቆያሉ፡፡ አገሪቱን አቶ ኃይለ ማርያም እስከ 2007 ብሔራዊ ምርጫ ድረስ እየመሩ እንደሚቆዩ የገለጹት አቶ በረከት፣ እስከዚያው ድረስ ምንም ዓይነት ምርጫ እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ሐምሌ 12 ቀን 1957 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ወላይታ ውስጥ የተወለዱ ሲሆን፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው አካባቢ ተምረዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የመጀመርያ ዲግሪያቸው በሲቪል ምሕንድስና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካገኙ በኋላ፣ በአርባ ምንጭ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሠርተዋል፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመት ከሠሩ በኋላ ፊንላንድ ከሚገኘው ቴምፕር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሳኒቴሽን ምሕንድስና አግኝተዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የደቡብ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደሕዴን) ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ ከ2002 ብሔራዊ ምርጫ በኋላ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እንዲሠሩ ተሹመዋል፡፡ አቶ ደሳለኝ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ሦስት ልጆች አሏቸው፡፡ በቅርቡም ወይዘሮ ሮማን ቀጣይዋ የኢትዮጵያ ቀዳማዊ እመቤት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃሉ፡፡ ወይዘሮ ሮማን በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ውስጥ የሰብዓዊ መብት መከበር ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነው ይሠሩ ነበር፡፡ ወይዘሮ ሮማን በአመራርና በኢኮኖሚክስ ሁለት የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ መለስ ታላቅ መሪ ነበሩን? ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከ19 ዓመታቸው ጀምሮ ዕረፍት እንደማያውቁ ገልጸው፣ ዕረፍት የሚባለውን ነገር ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረፍ ቢፈልጉም በፓርቲያቸው ግፊት ሥራ ላይ እንደሚገኙ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡ ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ በሥራ ላይ የነበሩት መለስ፣ በተለይ በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው ሳያርፉ የመሞታቸው ጉዳይ አንገብጋቢ ሆኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ነበራቸው፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርም የኢትዮጵያን ጥቅም በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስጠበቅ ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ኃይለ ማርያም የመለስን ሥራ በማስቀጠል ከፊታቸው ወሳኝ ጊዜ ይጠብቃቸዋል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ አስተያየት ሰጪዎች አቶ ኃይለ ማርያም እስካሁን ዕድሉን ስላላገኙ የአመራር ብቃታቸው ምን እንደሚመስል ባይታወቅም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከሠሯቸው ሥራዎች በላይ ሊሠሩ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ታላቅ መሪ መሆናቸውም የሚታወቅው በእርሳቸው ጫማ የገቡት አቶ ኃይለ ማርያም ራዕያቸውን ማስፈጸም ሲችሉ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይህም በቀጣዮቹ ጊዜያት የሚታይ ይሆናል፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Ethiopian can not afford a prolonged war.
Ethiopian can not afford a prolonged war. Ethiopia as the poorest country in the world is dependent on aid. A prolonged war simply depletes ...
-
8/10/2012 The prolonged absence of Meles Zenawi, Ethiopia’s usually hyperactive prime minister, has sparked a covert succession struggle at ...
-
Addis Ababa, June 28 – Expansion project of Messebo Cement Factory that has been carried out at a cost of over 2.3 billion birr was i...
-
Wednesday, 29 August 2012 - African Development Bank approved a 251 million US dollar loan for Ethiopia. The two parties signed the loan agr...
No comments:
Post a Comment